Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመዲናዋ ነዋሪ ከተማውን በንቃት እንዲጠብቅ ከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ ሳምንታት የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የመዲናዋ ነዋሪ አካባቢውንና ከተማውን በንቃት ተደራጅቶ እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ÷ የመዲናዋ ነዋሪ ከፀጥታ ኃይሉ እና ከሰላም ሰራዊቱ አደረጃጀት ጋር በመተባበር ከተማውን እና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ፣ ፀጉረ ልውጦችን፣ የሽብር ወሬ የሚነዙና የኢኮኖሚ አሻጥር ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም የተለያዩ ሕዝባዊና መንግስታዊ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎሉ የሚያደርጉ አካላትንም ለፀጥታ ኃይሉ በማጋለጥ ነዋሪው ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስተዳደሩ አሳስቧል፡፡

በጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አኩሪ ተጋድሎ የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ላንቃ እየተዘጋና ወረራው በብቃት እየተመከተ መሆኑን መግለጫው አውስቷል፡፡

ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አድናቆት አለው ያለው መግለጫው÷ “ምንጊዜም ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናችንን በተግባር እያረጋገጥን ኃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን” ብሏል፡፡

“በአማራና አፋር ንፁሃን ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት ተግባራዊ በማድረግ እንቀጥላለን” ነው ያለው አስተዳደሩ፡፡

አሸባሪው ህወሓና ተላላኪዎቹ በተደጋጋሚ አዲስ አበባን ለማተራመስ፣ የሽብርና የእርስ በእርስ እልቂት ውስጥ ለመክተት የማያባራ ሙከራ ሲያደርጉ መቆየቱን ያስታወሰው መግለጫው÷ “አሁንም ይህንኑ ቅዠታቸውን ለመፈፀም ሲጥሩ ተስተውሏል” ብሏል፡፡

ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና አንድነትን የሚበትኑ መረጃዎች በማሰራጨት፣ በከተማዋ ውስጥ የሽብር ቡድኖቹ የህወሓትና የሸኔን የተለያዩ የፅንፍ አስተሳሰብ የሚረጩ አባላትን በማስረግና የጥፋት ሴሎችን በማደራጀት፣ ሰላምን ለማወክ፣ የጸጥታ ስጋት ለመፍጠርና የእኩይ እቅዳቸውን ለማሳካት በግልጽ እንቅስቃሴ እያካሄዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም የሽብር ቡድኑ በዘረጋው የሌብነትና የዝርፊያ አደረጃጀት አስርጎ ባስገባቸው ተላላኪዎች ተጠቅሞ በተለያዩ ወንጀሎችና የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈፀም፣ ህብረተሰቡን በማማረር መንግስት ላይ ጫና ማሳደር በሚለው ያረጀ ስልት ለመጠቀም ጥረት እያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በስልቶቹም በየቦታው ሕገ ወጥነትን ማስፋፋትና የመሬት ወረራ እንዲካሄድ፣ የፖለቲካ ግብ ያላቸው የደረቅ ወንጀሎች እንዲስፋፉ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የኑሮ ውድነት እንዲባባስና ሕዝቡ አንዲማረር ለማድረግ የቀን ቅዠታቸውን ለማሳካት ግብ ያደረጉ እንቅስቃሴዎቻቸው በየአካባቢው መታየት ጀምረዋል ነው ያለው መግለጫው፡፡

የሽብር ቡድኑ በህዝብ ውስጥ ሊሸሸግ የሚያስችለው እድል እንደሌለው ቢታመንም÷ በማንኛውም ሁኔታ የዚህ እኩይ ተግባር ተሳታፊ ሆነው የተገኙ አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብሏል መግለጫው፡፡

የመዲናዋ ነዋሪም÷ ወቅታዊ የኑሮ ጫናን ለማቃለል ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የከተማ አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ በኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል እንዲቀርብ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን አውቆ ለህገወጦች እቅድ ተጋላጭ ከመሆን ራሱን እንዲጠብቅ አስተዳደሩ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

አስተዳደሩ እና ህዝቡ ከግንባር እስከ ደጀን ለሰራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ሁሉም በተሰማራንበት ውጤታማ በመሆን የእኩይ ሴራዎችን በማክሸፍ፣ የመዲናዋን ሰላም ዘላቂነት በማረጋገጥና ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ በተደራጀና በተቀናጀ አመራር ከሕዝቡ ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን እንደሚቀጥልም አስተዳደሩ በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡

Exit mobile version