የሀገር ውስጥ ዜና

የህወሓትን ዳግም ወረራ አወግዛለሁ – የእስራኤል የፐብሊክ ጉዳዮች ማዕከል

By Mikias Ayele

September 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት የፈፀመውን ዳግም ወረራ እንደሚያወግዙ የእስራኤል የፐብሊክ ጉዳዮች ማዕከል የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዳን ዲከር ተናገሩ፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ከእየሩሳሌም የፐብሊክ ጉዳዮች ማዕከል የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዳን ዲከር ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ረታ በውይይቱ፥ መንግስት ብሔራዊ ውይይት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የወሰዳቸውን እርምጃዎች አብራርተዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ የሰላም አማራጮችን ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሸባሪው ህወሓት ይህንን የመንግስት የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ሦስተኛ ዙር ጦርነት በመክፈት ንፁሃን ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡

የእየሩሳሌም የፐብሊክ ጉዳዮች ማዕከልም የዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ተቋማትና አካላት የኢትዮጵያ መንግስት  እያደረገ ያለውን የሰላም ጥረት እንዲደግፉና የሽብር ቡድኑን ድርጊት እንዲያወገዝ ጠይቀዋል።

ዳን ዲከር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ እንዲሻሻልና መንግስት ሀገራዊ ሰላም ለማምጣት የሰጠውን ትኩረት በማድነቅ÷ ትህነግ ዳግም ጦርነት ከፍቶ እያደረሰ ያለው ውድመት አስከፊና የሚወገዝ መሆኑን ገልፀዋል።

የህወሓትን የሽብር ተግባርም ለተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት እናደርሳለን ማለታቸውን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያና የእስራኤልን ወዳጅነት ለማጠናከር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡