አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ጨዋታዎች፣ የስፖርት ፌስቲቫል፣ ስልጠናዎች፣ ጉባኤዎች እና ትላልቅ ስብሰባዎች ለ15 ቀናት በየትኛውም ቦታ እንደማይካሄዱ አስታወቀ።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውድድሮች እና የስልጠና መድረኮች ለህዝቡ ደህንነት ሲባል በቫይረሱ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ በመንግስት እስከሚሰጥ ድረስ እንደማትሳተፍም አስታውቋል።
ከዛሬ ጀምሮም በመንግስት አስፈላጊው መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ ምንም ዓይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻል መግለጹን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በኮሚሸኑ አዘጋጅነት በማህበረሰብ ስፖርት ተሳትፎ እና በስፖርታዊ ጨዋነት ማስፈን ዙሪያ መጋቢት 9 እና 10 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የባለድርሻ አካላት መድረክ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በበኩሉ በስር የሚገኙ ማዕከላትና የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አረጋይ ዛሬ ለዝግጅት ከፍላችን በሰጡት መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ በአራት ኪሎ ስፖርት ትምህርት ስልጠና ማዕከል፣ በጃንሜዳ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል፣ በራስ ሀይሉ ስፖርት ትምህርት ስልጠና ማዕከል እና በአዲስ አበባ ሜዳ ቴኒስ ማዕከል እንዲሁም በ117 ወረዳዎች በሚገኙ የስፖርት ማዝወተሪያዎች ማንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላልተወሰነ ጊዜ መቆሙን ተናግረዋል።
መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ታላላቅ ስብሰባዎች እንዲዘጉ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይካሄዱ ለ15 ቀናት መወሰኑ ይታወሳል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision