አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከባድ የሰው ግድያ፣ የግለሰቦችን ቤት በማቃጠል እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሣሪያን በመጠቀም ወንጀል የተከሰሰው ካሳሁን ተካልኝ የተባለው ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጣ፡፡
በሸካ ዞን ፍትሕ መምሪያ የቴፒ ምድብ ጽሕፈት ቤት ዐቃቤ ሕግ እንድሪስ እሸቱ እንደገለጹት÷ ተከሳሹ በሸካ ዞን በየኪ ወረዳና ቴፒ ከተማ ባለፉት ዓመታት ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ መደፍረስ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽሟል፡፡
ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ በኅብረት የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ከነበሩ ሰዎች ጋር በመሆን÷ ህዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም በየኪ ወረዳ ሰላም በር ቀበሌ ከቀኑ በግምት 7:30 አካባቢ የፌዴራልና የክልል ልዩ ኃይሎች የመንግሥት አመራሮችን አጅበው ሲጓዙ አራቱን የፀጥታ ኃይሎች መግደላቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል ብለዋል።
በተጨማሪም መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም በቴፒ ከተማ ኅብረት ቀበሌ ከምሽቱ 1:30 አካባቢ ሦስት ግለሰቦችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በ2013 ዓ.ም ቀኑ እና ዕለቱ በውል በማይታወቅበት በቴፒ ከተማ ኅብረት ቀበሌ መናኸሪያ አካባቢ አልጋ ይዘው ያደሩትን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ አባላት ወደ መኝታ ክፍላቸው በመግባት መግደላቸው ተመላክቷል፡፡
ተከሳሹ በኅብረት በተፈጸሙ ወንጀሎች ሙሉ በሙሉ ተካፋይ መሆኑ በሰውና ሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡
የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት ባስቻለው ችሎት ተከሳሹ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!