አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ96 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ አይሪን አስትበሪ እድሜ ሳይገድባቸው አሁንም በስራ ያሳልፋሉ፡፡
የዛሬ 36 አመት ከስራ በጡረታ የተገለሉት አዛውንት ከጡረታቸው በኋላ በእረፍት ቤተ ተቀምጠው ማሳለፍን ሳይሆን የራሳቸውን ስራ መስራትን ነበር የመረጡት።
ለዚህም በፈረንጆቹ 1981 ከሟች ባለቤታቸው ጋር በመሆን በቼሻየር አካባቢ ማክልስፊልድ ከተማ የሚገኝ የልብስ ንጽህና መስጫ ቤት (ላውንደሪ) በመግዛት ነበር ስራ የጀመሩት።
በወቅቱ የገዙትን ይህን የልብስ ንጽህና መስጫ ቤት በሂደት ለቤት እንስሳት ምግብ አቅራቢ መደብርነት በመቀየር ስራቸውን መቀጠላቸውን ይናገራሉ።
ለአራት አስርት ዓመታትም አይሪን ከዚህ ስራቸው ሳይለዩ በሱቃቸው ውስጥ በታታሪነት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት አዛውንቷ እመቤት “በጡረታ ከተገለልኩ 36 ዓመታት ቢያልፉኝም እኔ ግን ተስፋ ሳልቆርጥ ስሰራ ቆቻለሁ፣አሁንም መስራት እፈልጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“አሁንም ብርቱ እንደሆንኩ ይሰማኛል” የሚሉት አይሪን አሁን ከሚሰሩበት የስራ ጊዜ የበለጠ መስራት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ወጣቶች ኩባንያ ላይ ተቀጥረው መስራት ይችላሉ የሚሉት አዛውንቷ አይሪን፥ የእድሜ ባለፀጎች ግን ከኩባንያ የቅጥር ስራ ባለፈ የግል ስራ ማከናወን እንደሚችሉም ይመክራሉ፡፡
“ቤት ቁጭ ብየ ብውል ምን ሊኖር ይችል ነበር?” ሲሉ የሚጠይቁት የእድሜ ባለፀጋዋ ተንቀሳቀሰው በመስራታቸው ሁሉንም ነገር ማየት መቻላቸውንም ነው የሚያስረዱት።