አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በአሜሪካ የቀረበውን የነዳጅ ዋጋ ገደብ ለሚደግፉ ሀገራት ነዳጅ ላታቀርብ እንደምትችል አስጠነቀቀች።
በቅርቡ የቡድን 7 ሀገራት ባደረጉት ስብሰባ አሜሪካ በነዳጅ ዋጋ ላይ ገደብ እንዲጣል ሃሳብ አቅርባለች።
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክም ይህን እቅድ የሚደግፉ ሀገራት የሩሲያን ነዳጅ ላያገኙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ቡድኑ አሜሪካን ጨምሮ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓንን ያካተተ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ገደቡንም ከንቱ ሃሳብ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
አሜሪካ የተባባሰውን የሃይል አቅርቦት ዋጋ ለማረጋጋት በሚል ገደቡ እንዲጣል ሃሳብ ታቅርብ እንጅ በርካቶች ግን በማዕቀብ የታሰበውን ያክል አልተጎዳም የተባለውን የሩሲያን ኢኮኖሚ ለመጉዳት ያሰበ ነው በሚል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሃላፊ ጃኔት የለን የዋጋ ማሻሻያ የዋጋ ንረትን ለመዋጋት እንደሚረዳ ጠቅሰው፥ ይህ መሆኑ የተረጋጋ የነዳጅ ፍሰት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ ያግዛል ብለዋል፡፡
ኖቫክ በበኩላቸው የሩሲያ የነዳጅ አምራቾች በታህሳስ ወር በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ላይ ለመተግበር ለታቀደው የነዳጅ ማዕቀብ እየተዘጋጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሩሲያ ወደ ውጭ የላከችው የነዳጅ ዘይት መጠን ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ወር ድረስ መቀነሱን ሲ ጂ ቲ ኤን በዘገባው አመላክቷል።
ሆኖም የወጪ ምርት ገቢዋ ካለፈው ወር አንጻር በ700 ሚሊየን ዶላር ከፍ ብሎ 20 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ገልጿል፡፡
ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአማካይ ከ40 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ተሰምቷል፡፡
የቡድን 7 ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች በድጋሚ ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!