Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ከሶማሊያ አቻቸው ጋር በትብብር ለመስራት ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዶክተር በለጠ ሞላ በአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ በትብብር ለመስራ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሶማሊያ ሪፐብሊክ አቻቸው ጃማ ሃሰን ካሊፍ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትር በለጠ ሞላ በውይይታቸው÷ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበረው እና ነገ የሚካሄደው የአፍሪካ ቀንድን በኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የሚያስችለው ፕሮጀክት ኢትዮጵያንና ሶማሊያን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልፀዋል።

የሶማሊያ የኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጃማ ሃሰን ካሊፍ በበኩላቸው፥ በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በአመራሮች በኩል የተጀመረው ግንኙነት በባለሙያዎችም ተደግፎ ጠንካራ ተሞክሮዎች ላይ የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

በዘርፉ ውጤታማ ትብብር ለማድረግ ከሁለቱ ተቋሞች በተውጣጡ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቷል መባሉንም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version