ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአውሮፓ ህብረት የጋዝ ፍጆታውን ለመሸፈን ፊቱን ወደ ቻይና ማዞሩ ተነገረ

By Mikias Ayele

August 31, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ የሚቀርበው የጋዝ ሽያጭ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ አማራጭ ገበያ እያፈላለገ መሆኑን አስታውቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ህብረቱ የጋዝ ፍላጎቱን ለመሸፈን ፊቱን ወደ ቻይና ኩባንያዎች አዙሯል ነው የተባለው።

የዓለማችን ትልቋ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ገዢ የሆነችው ቻይና ካላት ክምችት ከፊሉን ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረበች መሆኗን ፋይናንሺያል ታይምስ አስነብቧል።

ህብረቱም ከቀዝቃዛው የክረምት ወቅት በፊት የኃይል ፍላጎቱን ለማሟላት ከቻይና በቀጥታ ግዢ ጋዝ ለመግዛት ማቀዱን አር ቲ በዘገባው አመላክቷል።

ግዢው የቻይና ኩባንያዎች ከሌሎች ሀገራት በግዢ ያከማቹትን የተፈጥሮ ጋዝ ለገበያ በሚያቀርቡበት ወቅት የሚፈጸም ሲሆን፥ ለህብረቱ አባል ሀገራትም ከሩሲያ ከሚገዙት አንጻር ውድ መሆኑም ነው የተነገረው።

በ2022 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተሸጠው አጠቃላይ የቻይና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ መጠን ከ4 ሚሊየን ቶን ከፍ ሊል እንደሚችል የፋይናንሺያል ታይምስ ግምታዊ መረጃ ያመላክታል።