አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ ተቋማት የህወሓትን ዝርፊያ ማጋለጣቸው ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ በር የሚከፍት መሆኑን ፖለቲከኞች ተናገሩ፡፡
ፖለቲከኞቹ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ድርጊቱ ህወሓት ቆሜለታለሁ ለሚለው ህዝብ እንኳን ጭካኔው እስከምን ድረስ እንደሆነ አስረጂ ነው ብለዋል።
የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አብድልቃድር አደም እና በኢዜማ የብሄራዊ ምክክር ኮሚቴ ሰብሳቢ እዮብ መሳፍንት የህወሓትን የዘወትር ተግባር በዓለም አቀፍ ተቋማት መገለጹ ፣ የኢትዮጵያን ቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራ ያቀላል ነው ያሉት።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሀፊዋና የሶዴፓ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ራሂል ባፌ በበኩላቸው÷ ቡድኑ የሚያራምደው ዓላማ ጸረ ሕዝብነቱን ያረጋገጠ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ፖለቲከኞቹ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከማውገዝ ባለፈ ወደ እርምጃ እንዲገባ ጠንከር ያለ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
አሸባሪው ህወሓት መቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን ውስጥ በሀይል በመግባት 12 የነዳጅ ቦቴዎችን በአጠቃላይ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉን ተመድ መግለፁ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎም አሸባሪው ህወሓት የፈፀመው ዝርፊያ አስፀያፊ እና አሳፋሪ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌ መናገራቸውና ማውገዛቸው ይታወሳል ፡፡
ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡
በሙሃመድ አሊ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!