Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የግብርና ግብዓቶች እየተሰራጩ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፀረ አረም እና ተባይ መከላከያ የኬሚካል ግብዓት አቅርቦቶች ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ መሆኑን ክልሎቹ አስታወቁ።

በመኽር የተዘራው ሰብል ምርታማነት እንዳይቀንስ የግብርና ባለሙያዎችን በማሰማራት ክትትል እያደረጉ መሆኑንም ነው የክልሎቹ የሥራ ኃላፊዎች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ÷ የአረም ክትትል በስፋት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ለማቅረብም ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነው አቶ መስፍን የተናገሩት።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፈ÷ በክልሉ ለአርሶ አደሩ የኬሚካል አቅርቦት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የፀረ አረም ኬሚካል ለሚያስፈልጋቸው ሰብሎችም ፈቃድ ባላቸው አቅራቢ ድርጅቶች ወደ 19 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ኬሚካል እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ሰብሉን በመንከባከብና በመከታተል ምርታማነትን ማሳደግ እንዳለበትም የሥራ ኃላፊዎቹ አሳስበዋል።

በዙፋን ካሳሁን

Exit mobile version