አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች በአውሮፓ ውስጥ የግዙፍ ዳይኖሰር ቅሪተ አካል ማግኘታቸውን አስታወቁ።
የፖርቹጋል እና የስፔን ተመራማሪዎች ቡድን ነው በፖርቹጋል በሞንቴ አጉዶና ፖምባል ውስጥ ቅሪተ አካሉን በቁፋሮ አገኘሁ ያለው፡፡
የተገኘው የዳይኖሰር ቅሪተ አካል ብራሺዮሳዩሪድ ሳውሮፖድስ ዳይኖሰር በመባል የሚታወቁ ሲሆኑ ፥ ግዙፍ አካል ፣ ረዥም አንገትና ጅራት ያላቸው ባለአራት እግር እጽዋት ተመጋቢ የዳይኖሰር ዓይነቶች እንደሆኑ ተነስቷል፡፡
ከተገኙት ቅሪቶች በመነሳትም ተመራማሪዎቹ ዳይኖሰር 12 ሜትር (39 ጫማ) ከፍታ እና 25 ሜትር (82 ጫማ) ርዝመት እንዳለው ይገምታሉ።
ቡድኑ እስካሁን ድረስ የአከርካሪ አጥንቶችን እና የጎድን አጥንቶችን ጨምሮ ጠቃሚ የቅሪት አካል ክፍሎችን ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡
በሊዝበን ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ የድህረ ዶክትሬት ተመራማሪ የሆኑት ኤልሳቤት ማላፋያ ፥ “መሰል የእንስሳት የጎድን አጥንቶችን በዚህ ቦታ ማግኘት የተለመደ ነገር አይደለም” ብለዋል ።
በዚህም እነዚህ የዳይኖሰር ዓይነቶች ከ160 እስከ 100 ሚሊየን ዓመታት በፊት በላይኛው ጁራሲክና የታችኛው ክሪቴሴየስ ዘመን መካከል ይኖሩ እንደነበርም ነው የተነሳው፡፡
ሆኖም የዳይኖሰር ቅሪተ አካል በአውሮፓ ሲገኝ የመጀመሪያው አይደለም።
በሰኔ ወር ላይ የስፒኖሳውሪድ ቅሪተ አካል ከእንግሊዝ በስተደቡብ በምትገኝ ደሴት መገኘቱን ሲኤንኤን በዘገባው አስታውሷል።
በተጨማሪም 11 ሜትር (36 ጫማ) ርዝመት ያለው ከቲራንኖሳውረስ ሬክስ ክንድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አዲስ ሥጋ በል የዳይኖሰር ዝርያ በሰሜናዊ ፓታጎንያ አርጀንቲና መገኘቱን ሳይንቲስቶች ባለፈው ወር አስታውቀዋል።
ታይራንኖሰርስ ቴሮፖድ በመባል የሚታወቅ ግዙፍ የዳይኖሰር ዝርያ ነው።
በፖምባል የተገኘው ቅሪተ አካል በቦታው ላይ ተጨማሪ ቁፋሮ በማካሄድ የበለጠ ሊገኝ እንደሚችል ያመላክታል፡፡