Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብሪታሚያ ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ዜጎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ልታስገባ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሪታኒያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎችን ለአራት ወራት  ወደ ለይቶ ማቆያ ልታስገባ መሆኑ ተገልጿል።

ከአራት ወር በፊት  በቻይና የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ አሁን ላይ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዛመት ላይ ይገኛል።

በተለይም በአውሮፓ ሀገራት የቫይረሱ ስርጭት መጠን የከፋ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በሀገራቱ እስከ ዛሬ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቀን ከተመዘገበባቸው የሞት መጠን አንጻር ትናንት ከፍተኛ የተባለውን ሞት መመዝገቡ ተመላክቷል።

በዚህ መሰረት በጣሊያን በትናንትናው ዕለት ብቻ 368 ዜጎች በቫይረሱ ህይወታቸው ሲያልፍ፥ አጠቃላይ ለህልፈት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 1 ሺህ 809 ደርሷል።

በቫይረሱ ከቻይናቀጥላ  ከፍተኛ  ጉዳት በደረሰባት ጣሊያን በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ወደ 25 ሺህ አሻቅቧል።

በተመሳሳይ በብሪታኒያ ትናንት ብቻ 14 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥርም ወደ 35 ከፍ ብሏል።

ይህን ተከትሎም  ሀገራቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ትምህርት ቤቶች፣ ስብሰባዎች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲዘጉ ከማድርግ ባለፈ  የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው።

ብሪታኒያ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከ 70 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ ዜጎቿን ለአራት ወራት ወደ ለይቶ ማቆያ ልታስገባ መሆኑ ተሰምቷል።

እቅዱ የኮሮና ቫይረስ በእድሜ የገፉ ሰዎችን የማጥቃት ዕድሉ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቀረበ መሆኑን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ምንጭ፦ቢቢሲ

 

 

 

 

Exit mobile version