አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በዘመን መለወጫ በዓል ሰሞን የሚያስፈልጉ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፆኦ ውጤቶች ጨምሮ ሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እጥረት እንዳይኖር እየተሠራ መሆኑ የከተማዋ የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በዘመን መለወጫ በዓል ለነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፆኦን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በሸማች ማህበራት በኩል እንዲቀርቡ እየተሠራ ነው ብሏል ኤጀንሲው፡፡
ይቀርባሉ ከተባሉት ምርቶች መካከል፥ ቀይ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የበቆሎ ዱቄት፣ዶሮና እንቁላል፣ ቅቤና አይብ ይገኙበታል።
ምርቶቹ ከበዓሉ አስቀድሞ ባሉ ቀናት 148 በሚሆኑ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት የሚቀርቡ መሆኑን የኤጀንሲው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጌታቸው ተናግረዋል።
ከ225 በላይ የሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች ለቅርጫ የሚሆኑ በሬዎችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት አድርገዋል ነው የተባለው።
በገበያው ምንም አይነት የምርት እጥረት አለመኖሩ እየታወቀ የገበያ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩ አካላት ሲያጋጥሙ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ሃላፊው ጠቅሰዋል።