አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይጀሪያ መንግስት በቦኮሃራም ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ በሺህ የሚቆጠሩ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመልስ ፕሮግራም አስጀመረ።
ፕሮግራሙ በሰሜን ምስራቃዊቷ የቦርኖ ግዛት የሚተገበር ሲሆን፥ በግዛቷ በአሸባሪው ቦኮሃራም ከትምርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት የሚመልስ ነው።
ለዚህ ይረዳ ዘንድም ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን የቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ ያመላክታል።
እስካሁን 7 ሺህ የ1ኛ እና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ተመዝግበዋል ነው የተባለው።
በፕሮግራሙ በዋናነት በአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ህጻናት ተጠቃሚ ይሆናሉም ተብሏል።
በዚህ ፕሮግራም ከ20 ሺህ በላይ ህጻናትን ወደ ትምህርት ለመመለስ መታቀዱን የግዛቷ አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል።
ቦኮሃራም ከፈረንጆቹ ከ2009 ጀምሮ በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ እና በአጎራባች ሀገራት በሚፈጽመው ጥቃት በሺህ የሚቆጠሩትን ለህልፈትና ስደት መዳረጉን መረጃዎች ያመላክታሉ።