የሀገር ውስጥ ዜና

ጀግናው መከላከያ ሰራዊት አሸባሪውን የህወሓት ቡድን እንደ አመጣጡ አፀፋዊ ምላሽ እየሠጠውና እየደመሰሰው እንደሚገኝ አስታወቀ

By Mekoya Hailemariam

August 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ካለፈው የህልውና ዘመቻዎች የጠላትን አሠላለፍ በውል በመገንዘብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን እንደ አመጣጡ አፀፋዊ ምላሽ እየሠጠው እና እየደመሰሰው እንደሚገኝ አስታወቀ።

ሠራዊታችን የድል ሠራዊት ነው በሚል ባወጣው መግለጫ፥ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ፣ አስቸጋሪ መልክአ ምድርንም ሆነ የአየር ፀባይ ተቋቁሞ ግዳጁን በድል አድራጊነት የሚወጣው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፥ ጠላትን በአስተማማኝ መመከት የሚችል ኃይል መሆኑን አረጋግጧል።

ሠራዊቱ ከራሱ ይልቅ ህዝብን ያስቀደመ፣ ለሀገር እና ለህዝብ እራሱን አሳልፎ የሠጠ ብሔራዊ ኩራታችን ነው ብሏል።

ጠላቶቻችን ህዝባዊ ባህሪውን በውል ስለሚገነዘቡ ህፃናትንና ሴቶችን ከፊት አሰልፈው ክፍለ ዘመን ባለፈበት ጦርነት በህዝብ መአበል መዋጋታቸው የሠራዊታችንን አይበገሬነትና ጀግንነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁት እንደሆነ ገልጿል።

በመሆኑም ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ካለፈው የህልውና ዘመቻዎች የጠላትን አሠላለፍ በውል በመገንዘብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን እንደ አመጣጡ አፀፋዊ ምላሽ እየሠጠው እና እየደመሰሰው ይገኛል።

ጠላት ለዜጎቹ ደንታ እንደሌለው ባሳየው በዚህ የኋላ ቀር ጦርነት ሠራዊታችን በከፍተኛ ጥንቃቄ እና የኃላፊነት መንፈስ ግዳጁን እየተወጣ እንደሆነ በማመልከት፥ አሸባሪው ህወሓት በለኮሠው እሳት መልሶ እየለበለበው ይገኛል ብሏል።