አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የህወሓት የሽብር ቡድን የጀመረውን ጦርነት አቁሞ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪ አቀረበ።
ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን በተመለከተ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የክልሉ መንግስት እና ሕዝብ በምሥራቅ በኩል የህወሓት አጋሮች በሆኑት እንደ አልሸባብ ባሉ የሽብር ቡድኖች የሚሞከሩ ሙከራዎችን በማክሸፍ እና በመደምሰስ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከማስከበር ባሻገር በህወሓት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እንደሁልጊዜው ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጿል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን በተመለከተ ከሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ!
ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆነው አሸባሪው የህውሓት ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ በአማራ ክልልና በአፋር ክልሎች ላይ የከፈተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በፅኑ ያወግዛል።
አሸባሪው የህውሓት ቡድን ለ27 ዓመታት የአገሪቱን ማእከላዊ ስልጣን ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ኢሰብዓዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ በአገሪቱ ህዝቦች መካከል እርስ በርስ መተማመን እና መተባበር እንዳይኖር የሚያደርግ ጥላቻ በመንዛት የከፋ ስቃይና መከራ ያደረሰ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ቡድኑ የአገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ በነበረበት ዘመን የሶማሌ ክልል ህዝብን ገድሏል፤ አፈናቅሏል ፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ተቆጥረው የማያልቁና ለማመን የሚከብዱ ዘግናኝ የጭካኔ ተግባራትን ሁሉ አንድም ሳያስቀር ፈፅሟል፡፡
ከዚህም አልፎ ለርካሽ ፖለቲካና ለስልጣኑ ቀጣይነት ሲል ሴራ በመጎንጎን የሶማሌ ህዝብ ለዘመናት አብረው ከኖሩት ኢትዮጵያዊ ወንድም እህቶቹ ጋር እንዲጋደልና ደም እንዲቃባ አድርጓል፤ የክልሉን ሃብት በመዝረፍ እና የጥቂት ሰዎች ኪስ ማደለቢያ በማድረግም ክልሉ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጓል፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን ባለፈው ግፍና በደሉ ከመፀፀት ይልቅ አሁንም የሶማሌ ክልልን በማተራመስ ህዝቡ ያገኘውን ሰላምና ነፃነት ለመንጠቅ በአንድ በኩል በክልሉ አዋሳኝ ከሚገኙ ወንድም ሕዝቦች ጋር ሰላም እንዳይኖረው ግጭት በመጥመቅ፣ በሌላ በኩል ከአልሸባብ ጋር ያልተቀደሰ የጥፋት አጋርነት በመፍጠር ክልሉን የማተራመስ እና አገር የማፍረስ ቅዠቱን ለማሳካት እየተራወጠ ይገኛል።
አሸባሪው ህውሓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየተጋለበ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚኖሩ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት አጥፍቷል፤ በእድሜ ልክ ድካም የተከማቸ የሚሊየኖችን ሃብትና ንብረትም በከንቱ አውድሟል።
የዚህ ባንዳ ቡድን ዋነኛ ሀሳብ ኢትዮጵያን እኔ ወይም የኔ ተላላኪ የሆነ ሀይል ካልመራት አፈርሳታለሁ የሚል ሲሆን ይህን በጤነኛ አእምሮ ሊታሰብ የማይችል ከክፋት ሁሉ የከፋ ሀሳቡን ለማስፈፀምም ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ምስኪን የደሀ ልጆችን በአደንዛዥ እፅ እያደነዘዘ ወደ እሳት እየማገደ ይገኛል።
ቡድኑ የያዘው እኩይ አላማ ለአገራችን ሁለንተናዊ ሰላም እና ልማት ፀር መሆኑን የሚገነዘበው የሶማሌ ክልላዊ መንግስት እና ህዝብ በምስራቅ በኩል የህወሓት አጋሮች በሆኑት እንደ አልሸባብ ባሉ የሽብር ቡድኖች የሚሞከሩ ሙከራዎችን በማክሸፍ እና በመደምሰስ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከማስከበር ባሻገር በህወሃት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እንደሁልጊዜው ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በአፅንኦት እየገለፀ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ያረጋግጣል፡፡
በመጨረሻም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት አቁሞ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም
ጅግጅጋ