የሀገር ውስጥ ዜና

ለአሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል- ላውረንስ ፍሪማን

By Melaku Gedif

August 28, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ፡፡

አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን እንዳሉት÷ አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ድጋፍ የሚደረግለት በመሆኑ በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ በመግፋት ዳግም ጦርነት ከፍቷል።

ከፌደራል መንግስት የቀረበለት የሰላም አማራጭ ሂደት ላይ እያለ ወደ ዳግም ጦርነት መክፈቱ ቡድኑ የውጭ ድጋፍ እንዳለው የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

በምርጫ ስልጣን ይዞ ሕዝብ እየመራ ያለውን የፌዴራል መንግስት ባለመቀበል፥ የጦርነት አዙሪት ውስጥ የገባው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እኩይ ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር አፍራሽ እቅድ የሚደግፉ አካላት የግጭቱ አባባሽና የጥፋቱ ተባባሪ ከመሆን ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የአሸባሪውን አገር የማፍረስ እኩይ ተግባር አይቶ ዝም ከማለት ይልቅ ማውገዝ እንዳለበት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ድንበሯን ጥሶ በመግባት ለአሸባሪው ህወሓት የጦር መሳሪያ ሊያቀብል የነበረ አውሮፕላን መትታ መጣሏ ተገቢ መሆኑንም ነው ላውረንስ ፍሪማን ያስረዱት።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!