አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመንግስት የቀረቡለትን በርካታ የሰላም አማራጮች ሁሉ ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኑ ህወሓት፥ ሲፈጽም የሰነበተውን ትንኮሳ ገፍቶበት የትግራይ ክልል በሚዋሰንባቸው የአማራና አፋር ክልሎች አካባቢዎች ሰፊ ጥቃት መክፈቱን መንግስት ገልጿል።
አሸባሪው ህወሓት የተለመደውን የሰው ማዕበል በመጠቀም የትግራይን ሕፃናት እና ወጣቶች ወደ እሳት እየማገዳቸው ይገኛል።
እየወጡ ያሉ የምስል መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት፥ የሽብር ቡድኑ ከ12 ዓመት ጀምሮ እድሜ ያላቸው ሕፃናትን የጦር መሳሪያ በማስያዝ ጥቃት በከፈተባቸው አካባቢዎች ከፊት እያሰለፈ የእሳት ራት እንዲሆኑ እያሰገደዳቸው ነው።
ያረጀ የጦርነት ስልት የሆነውን የሰው ማዕበል በመጠቀም ሕፃናቱን ከፊት አሰልፎ የጥይት ቀለብ እያደረጋቸው እንደሚገኝም ተገልጿል።
የኢፌዴሪ መንግስት፥ አሸባሪው ኃይል የትግራይን ወጣት እየማገደ በሕዝብ ማዕበል ማጥቃቱን ካላቆመ መከላከያ ሕጋዊ ፣ ሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታውን ለመወጣት እንደሚገደድም አሳስቧል።
በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሽብር ቡድኑ ህወሓት ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ የጦር ወንጀል እየፈፀመ መሆኑን አንስተዋል።
ይህን የሽብር ቡድኑን የጦር ወንጀል ድርጊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለምን ዝም አለ? ሲሉም እየጠየቁ ይገኛሉ።