አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶች አደባባይ በሚል የሰየመውን ፓርክ በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ፡፡
በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች ባስተላለፉት መልእክት፥ “ኢትዮጵያ የወጣት ሃገር ናት፤ ወጣቶቿ ደግሞ የዛሬም የመጪው ዘመን ተስፋዎቿ ናቸው” ብለዋል፡፡
ስለሆነም በምንሰራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ስራዎች የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያረጋገጥን መሄድ ሃላፊነታችንም ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡
“በአዲስ አበባ በርካታ አደባባዮችን ስናድስና አዳዲስ ስንገነባ፥ በአብዛኛው ስያሜ አላቸው፡፡ በጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ስም፣ በሴቶች ስም እና በህፃናት ስም አደባባዮች አሉ” ያሉ ሲሆን፥ በወጣቶች ስም ግን እስካሁን አልነበረም ብለዋል፡፡
“ወጣቶች በሃገር ግንባታ ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ከማዘጋጃ ቤት በቅርብ ርቀት በሚገኘው እና መሃል ከተማ ያለውን አደባባይ በእናንተ ስም ሰይመናል ከዛሬ ጀምሮ የእናንተ ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሰላም የሚተጉ፣ ለሰላሟ መስዋእትነት የሚከፍሉ ልጆች ያሏት አገር ናት፤ ያሉት ከንቲባ አዳነች፥ ሁሉም ወጣቶች ለሃገራቸው በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።