አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ለ2015 በጀት አመት 19 ቢሊየን 932 ሚሊየን ብር አፅድቋል።
ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፥ የክልሉን የ2015 በጀት አመት በጀትን 19 ቢሊየን 932 ሚሊየን ብር እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በጀቱ ከፌደራል መንግስት ድጋፍ፣ ከክልሉ የውስጥ ገቢና ከተለያዪ የገቢ ምንጮች የሚሰበሰብ ነዉ ተብሏል።
ለክልል ማዕከል፣ ለወረዳና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በድምሩ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ ነው የፀደቀው።
574 ሚሊየን ብር በላይ ለመሠረተ ልማት፣ ለዞን አደረጃጀት 150 ሚሊየን የፀደቀ ሲሆን፥ 185 ሚሊየን የክልሉ ተጠባባቂ በጀት ሆኗል።
የ2015 በጀት አመት እቅድ ተግባሮች የህዝብን ችግር መሠረት ያደረጉ ናቸው ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፥ የንግድ ስርዓቱን መስመር ማስያዝ፣ ስራ አጥነትና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ማፋጠን በጥብቅ ዲስፒሊን የሚተገበሩ ተግባርት ናቸው ብለዋል።
የዞን መዋቅርን በተመለከተ የዞን አደረጃጀት አስፈላጊ በመሆኑ ለወራት በተደረገ ጥናት መሠረት ከሐዋሳ በተጨማሪ አራት ዞኖች መደራጀታቸውን ገልፀዋል።
ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት ሲያካሔድ የነበረውን 6ኛ ዙር ምርጫ 1ኛ የስራ ዘመን 3ተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አጠናቋል።
በተጨማሪም የክልሉ ምክር ቤት የሲዳማ ክልል በአራት ዞኖች እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
እንዲሁም በክልሉ በሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ላይ የአስተዳደር መዋቅር ምክር ቤት አባላትን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ አፅድቋል።
በተጨማሪም ክልሉ የዞን መዋቅር በሁለት ተቃውሞ ድምፅና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል ።
በዚህም መሠረት ክልሉ አንድ ከተማ አስተዳደርና አራት ዞኖች የሚኖሩት ሲሆን ፥ ሰሜናዊ ሲዳማ፣ማዕከላዊ ሲዳማ፣ደቡባዊ ሲዳማ ዞን ፣ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን እና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ናቸው።
በመቅደስ አስፋውና በታመነ አረጋ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!