Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሩሲያ ህወሓት በዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘን የፈጸመውን የነዳጅ ዝርፊያ አወገዘች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት በዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ አስነዋሪና ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ተናገሩ።

በመቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ 12 ታንከር ወይም 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ በህወሓት መዘረፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ መግለጻቸው ይታወቃል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ ህወሃት የዘረፈውን ነዳጅ በአፋጣኝ እንዲመልስ የጠየቁ ሲሆን ፥ በነዳጁ መዘረፍ ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማሳለጥ እንቸገራለን ብለዋል።

በዚህ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ፥ በመጋዘኑ ውስጥ የነበረው የምግብና የነዳጅ ክምችት በአስችጋሪ ሁኔታ ለነበሩ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል እንደነበር ጠቅሰዋል።

በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግር ሰለባ ለሆኑ የትግራይ ማህበረሰብ መድረስ የነበረበት እርዳታ በሽብር ቡድኑ መዘረፉ ተቀባይነት የሌለውና አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ዘራፊዎቹ ነውረኛ ድረጊታቸውን ክደው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የትግራይ ህዝብ ለችግር ተዳርጓል የሚል የተለመደ ልፈፋቸውን እንደሚቀጥሉና የህዝብ ተቆርቋሪ ለመምሰል እንደሚሞክሩም ነው የገለጹት።

በህወሓት የሽብር ቡድን የተፈጸመውን ዝርፊያ የትኛውም የዓለም ማህበረሰብ የማይደግፈው ድርጊት ነው ብለዋል።

የተፈጸመውን ድርጊት ማውገዝ እንደሚገባ ጠቅሰው ፥ አንዳንድ ድርጊቱን በዝምታ የሚያልፉ አካላትም እውነታው በገሃድ መውጣቱ እንደማይቀር ማወቅ አለባቸው ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version