አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዘመን መለወጫ በዓል የተለያዩ ምርቶችን በተሻለ ዋጋና አቅርቦት በብዙ አማራጮች ለህብረተሰቡ ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ገለጸ።
ከመጪ በዓላት ጋር ተያይዞ አስፈላጊ በሆኑ ምርቶች ላይ እጥረት እንዳያጋጥም ከወዲሁ የአቅርቦት ስራው በሰፊው በመከናወን ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ገልጿል።
የኤጀንሲው የገበያ ጥናትና ማስፋፊያ ዳይሬክተር ደብሪቱ ለዓለም እንዳሉት ለበዓላቱ በተለይም የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳያጋጥም ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም÷ በመዲናዋ የሸማች የህብረት ስራ ማህበራት፣ የእሁድ ገበያ እና አጠቃላይ ግብይቶች ሰፊ አቅርቦት እንደሚኖር ጠቁመዋል።
የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች እንዲሁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ለህብረተሰቡ በብዛትና በጥራት ይቀርባሉም ነው ያሉት።
በህብረት ስራ ከሚቀርቡ ምርቶች በተጨማሪ ኤጀንሲው የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ የህብረት ስራ ማህበራት ጋራ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሸማች ማህበራት ለህብረተሰቡ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች በተገቢው መልኩ ተደራሽ እንዲሆኑ የድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚከናወንም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባለፈም የምርት እጥረት ሳይፈጠር የገበያ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩ አካላት ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡