የሀገር ውስጥ ዜና

በ2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

August 25, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት ቀጣይነት ባለዉ የልማት ግብ የተያዘዉን ዕቅድ ማሳካት እንደሚያስፈልግ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ÷ ተገቢዉን ትኩረት ሳያገኝ የቆየዉ የሕጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ልይታ፣ ምርመራና ሕክምና ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዶ/ር ሊያ ታደሰ ÷ በሎሜ ቶጎ እየተካሄደ ባለዉ 72 ኛው የአፍሪካ አኅጉር የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሯ በመግለጫቸው በኢትዮጵያ በ2015 የጸደቀዉ የሕጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ሕጻናትና አፍላ ወጣቶችን ከቲቢ በሽታ የመከላከልና ሕክምና ሥራ መሻሻሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለማችን የቲቢ እንዲሁም ቲቢ-ኤች አይቪ ሥርጭት ይበልጥ ከተስፋፋባቸዉ 30 ሀገሮች አንዷ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም የሚሰሩ ስራዎች ለቲቢ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑና የተዘነጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ትኩረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በፈረንጆቹ 2030 የቲቢ በሽታን ለመግታትም ከሰሃራ በታች ያሉ በቲቢ በሽታ ስርጭት ይበልጥ የተጎዱ ሀገራትንም ማገዝ እንደሚገባ ዶ/ር ሊያ አሳስበዋል፡፡

ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ እና የተያዘዉን የዓለም ጤና ድርጅት አጀንዳ ከግብ ለማድረስ ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነዉም ብለዋል፡፡

ለዚህ ስራ ስኬትም በተለይ የበለጸጉ ሀገራት፣ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግብዓት እጥረት ያለባቸዉን ድሃ ሀገራትን እንዲረዱም ጥሪ ማቅረባቸውን ከጤና ሚኒስቴር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።