አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት መቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን ላይ የፈፀመው ዝርፊያ እንዳሳሰባት አሜሪካ ገለፀች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፥ ታጣቂ ቡድኑ ትናንት ጠዋት ላይ መቀሌ ወደሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን በሀይል በመግባት 12 የነዳጅ ቦቴዎችን በአጠቃላይ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ ዋሽንግተንን እንዳሳሰባት ጠቁሟል።
የነዳጅ ምርቱ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የነብስ አድን ቁሳቁሶች ለማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።
ለዜጎች የሚደረግ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን የሚከላከል ማናቸውንም ድርጊቶች አሜሪካ እንደምታወግዝም አስታውቋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌም ባወጡት መግለጫ፥ ህወሓት መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን ላይ የፈፀመው ዝርፊያ አስፀያፊ እና አሳፋሪ መሆኑን ነው የተናገሩት።