አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትዊተር “የደኅንነት ሥጋት” እንዳለበት አንድ የኩባንያው የቀድሞ የደኅንነት ክፍል ኃላፊ ማጋለጣቸው ተሰምቷል፡፡
የቀድሞው የደኅንነት ክፍል ኃላፊ በሰጡት የምሥክርነት ቃል ኩባንያው ለተጠቃሚዎቹ እና ለአሜሪካ የደኅንነት ተቆጣጣሪዎች የደኅንነት ክፍተት እንደሌለበት በማስመሰል ራሱን ይገልጻል ብለዋል።
ፔይተር ዛትኮ የተባሉት ግለሰብ በትዊተር የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ላይ ምን ያህል የተጭበረበሩ የግለሰብ ገፆች እንዳሉ ኩባንያው በግልፅ እንደማያውቅም ጠቁመዋል፡፡
ፔይተር ዛትኮ ባወጡት መረጃ “ትዊተር” ኤለን መስክን እንደዋሸው አጋልጠዋል፡፡
አሁን ላይ በቀድሞ ሰራተኛው በኩባንያው ላይ የቀረበው ውንጀላ ባለሃብቱ ኤለን መስክ ኩባንያውን በ44 ቢሊየን ዶላር ለመግዛት እያደረገ ባለው ጥረት ላይ እክል ሊፈጥር ይችላልም ነው የተባለው።
ትዊተር በበኩሉ የዛትኮን ውንጀላ የተሳሳተ ሲል አጣጥሎታል፡፡
ኩባንያው ፔይተር ዛትኮን በያዝነው ዓመት በፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ ደካማ በሆነ አመራራቸው እና በአፈጻጸም ጉድለት በግምገማ ከሥራ እንተሰናበቱም አስታውቋል።
እንደ ዛትኮ ገለጻ በትዊተር በርካታ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ግለሰቦች ገፆች ተጠልፈዋል።
ለአብነትም የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ጆ ባይደን እንዲሁም የዕውቁ ድምጻዊ ካንያ ዌስት ገፆች ተጠልፈዋል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ሁሉ የገጾች ጠለፋ ጀርባ ምናልባትም በትዊተር ኩባንያ ውስጥ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች እጃቸው ሳይኖርበት እንደማይቀር ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ በርካታ የትዊተር ተቀጣሪዎች የጥብቅ መረጃ ሥርዓቶችን እና የተጠቃሚዎችን መረጃዎች በቀላሉ ማግኘት መቻላቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ኩባንያው ገፃቸውን የዘጉ የማኅበራዊ ትሥሥሩ ተጠቃሚዎችን መረጃ በአግባቡ ማጥፋት አልቻለም ይህም ሌላው ጉድለቱ ነው ማለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።