Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ህብረተሰቡ የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲተገብር አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ህብረተሰቡ በጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲተገብር አሳስበዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፥ በትናንትናው እለት በሽታው በኢትዮጵያ መከሰቱን አስመልክቶ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፥ በኢትዮጵያ ተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሶስት ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ምዕመናን በጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲተገብሩ አሳስበዋል።

በቀሪው የዐቢይ ፆም ጊዜያት በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አድባራት እና ገዳማት የምህላ ጸሎት እንዲደረግም አውጀዋል።

የኮሮና ቨይረስ ባሳለፍነው ዓርብ በኢትዮጵያ በአንድ ጃፓናዊ ላይ የተገኘ ሲሆን፥ በትናንትናው እለትም ተጨማሪ ሶስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማስታወቁ ይታወሳል።

እስከ ትናንትናው እለትም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው 4 የደረሰ ሲሆን፥ ንክኪ የነበራቸው 183 ሰዎች ተለይተው የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑም ተገልጿል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

Back to top