የሀገር ውስጥ ዜና

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ

By Mekoya Hailemariam

August 21, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ።

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሠቦች በየዓመቱ ይህንን ሽልማት ይሰጣል።

ዶክተር ፍሬው ተገኘም በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እና በጃፓኑ ቶቶሪ ዩኒቨርስቲ መካከል ጠንካራ የአካዳሚክ ግንኙነት እንዲመሰረት አድርገዋል።

በእርሳቸው ጥረት ዩኒቨርስቲዎቹ የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም መብቃታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከ25 የሚበልጡ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች በተለያየ ጊዜ ወደ ጃፓን አቅንተው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉም አስችለዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ የጃፓን ዩኒቨርስቲዎች ጋር የጋራ ጥናትና ምርምር አድርገዋል።

እነዚህን ተግባራት በማከናወን ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጠናከር ላበረከቱት አስተዋፅኦ የ2022 ተሸላሚ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።