Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግስት የሰሜኑ ግጭት በሰላም እንዲቋጭ የዘረጋውን የሰላም እጅ እንደማያጥፍ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት የዘረጋውን የሰላም እጅ አስቸጋሪ ሁኔታ ካልመጣበት በስተቀር  እንደማያጥፍ አስታወቀ።

 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

 

በዚህ መግለጫቸውም በህወሓት የስግብግብነት እና ግትርነት ባህሪ  የተነሳ መንግስት  ሳይወድ በግድ ወደ ጦርነት የገባባቸውን ጊዜያት አስታውሰዋል።

 

መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ጦሩን ቢያወጣም ህወሓት ተጎራባች አካባቢዎችን በመውረር መንግስት ሳይወድ በግድ ወደ ጦርነት ገብቶ የታጣቂ ቡድኑን በወረራ ከያዘባቸው አካባቢዎች ማባረሩን ጠቁመዋል።

 

እንደዚሁም ለትግራይ ህዝብ ተጨማሪ እድል በመስጠት ከችግር  እንዲላቀቅ እና በአካባቢው መረጋጋት  ተፈጥሮ ራሱን መመገብ ወደሚያስችለው የግብርና ስራው እንዲመለስ መንግስት በራሱ ተነሳሽነት የተኩስ አቁም ማድረጉን ነው ያስረዱት።

 

በተጨማሪም ከግጭት  የሚገኝ ምንም  ነገር የለሌ በመሆኑ መንግስት ለትግራይ ሁለተኛ የጥሞና ጊዜ መስጠቱን አመልክተዋል።

 

የህወሓት ታጣቂ ቡድን መንግስት ግጭት ካቆመ በኋላ ተደጋጋሚ ትንኮሳም ሲያደርግ በሆደሰፊነት ማለፉን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

 

ይህንንም ያደረገው በራሱ እና ለህዝቡ  ካለው የሰላም ፍላጎት ነው ብለዋል።

 

አሁን ላይም ከመንግስት ወገን ምንም የተፈጠረ  አዲስ ነገር እንደሌለ  በማንሳት፥ “መንግስት የተኩስ አቁሙን አፍርሷል” የሚለው ክስ የህወሓት የሀሰት  ትርክት መሆኑን አስረድተዋል።

 

ይህንን የሀሰት ትርክቱንም  የእርሱ አፈቀላጤ በሆነው የዓለም ጤና ድርጅ ዋና ዳይሬክተር በኩል መቀጠሉን ነው በመግለጫው የተመለከተው።

 

ይህን የሀሰት ክስ ማምጣቱ ላቀደው እኩይ ተግባሩ ዓልሞ መሆኑን ተናግረው፥  የሀሰት ክሱም የሰላም አማራጭ  አለመፈለጉን ማሳያ መሆኑን ዶክተር ለገሰ ገልፀዋል።

 

ቡድኑ ሶስተኛ ዙር ጦርነት እየጎሰመ ያለው የለመደው በግጭት እና በሁከት  መኖር ስለሆነ እና የትግራይ ህዝብን ጥያቄ መመለስ ስለማይችል ነው ብለዋል።

 

መንግስት ግን አሁንም ለሰላም ያለው አቋም ፅኑ መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር፥ የሰላም ሀሳብን ማፅደቁን ጠቁመዋል።

በሰላም ሀሳቡ መሰረት መሰረታዊ አገልግሎት ለማስቀጠል አስተማማኝ ደህንነት እንደሚያስፈልግ እና ይህንንም ለማረጋገጥ የፖለቲካ ውይይት መጀመር እንደሚገባ መግለፁን ነው ያመለከቱት።

 

የጥፋት ቡድኑ ከጦርነት ናፋቂነት  ወደ ሰላም  አማራጭ እንዲመጣ እና የቀረበውን የሰላም እድል  እንዳያጣ የትግራይ ህዝብ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

 

ሸኔና አልሸባብ

 

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይል በተቀናጀ መልኩ አሸባሪው ሸኔ በመሸገባቸው አካባቢዎች እግር በእግር ተከታትለው እያጠቁ መሆኑን በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።

 

በዚህም ዘመቻቸው በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸው እና መማረካቸው እንዲሁም የስልጠና ማዕከላቱ መውደማቸውን ይፋ አድርገዋል።

 

የተበታተኑ የሽብር ቡድኑ አባላት በሸለቆዎች ውስጥ በመደበቅ  ንፁሃንን እያገቱ፣ ገንዘብ እየጠየቁና ንብረት እየዘረፉ በመሆኑ ለዚህ የማሸበር ተግባራቸው ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች እስከሚጠፉ ድረስ ዘመቻው እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

 

አልሸባበም ቢሆን በኢፌዴሪ የምድርና ዓየር ሃይል እንዲሁም በሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል የተቀናጀ ዘመቻ ቁሳዊ እና ሞራላዊ ሽንፈት መከናነቡን ተናግረዋል።

 

እነዚህ የሽብር ቡድኖች ሲሸነፉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ በመሆኑ ህዝቡ ይህን በመረዳት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

 

 

Exit mobile version