አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምረሃል በሚል ምክንያት የሦስት ልጆቿን አባት በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ትዕግስት አዘዘው የተባለቸው ግለሰብ ወንጀሉን የፈፀመችው መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አንቆርጫ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ተከሳሿ በዕለቱ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ የሦስት ልጆቿን አባት አወቀ ይርዳውን “ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምረሃል፤ የተለያዩ ሴቶችንም በስልክ ታወራለህ” በሚል ምክንያት ሶፋ ላይ በተኛበት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጓን በአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ከሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የከባድ ውንብድና እና ግድያ 1ኛ ወንጀል ችሎት ግለሰቧ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆኗን በማረጋገጥ÷ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ መወሰኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡