አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአራት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በሀገሪቱ አረንጓዴ ባህልን በመፍጠር ስኬታማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት ዓመታቱ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ መጠናቀቅን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ፥ “አሁንም ብዙ ስራ የሚጠበቅብን ቢሆንም፥ ንቅናቄው በሀገሪቱ ውጤት እንዳፈራ ግን ጥርጥር የለንም” ብለዋል።
ያለፉትን ጥቂት ሳምንታት ብቻ በዓለም ዙሪያ የተስተዋሉት የጎርፍ አደጋ፣ የደን ቃጠሎ፣ ሀይለኛ ማዕበል እና ያለተለመደ ሙቀትን የመሰሉ ሁኔታዎች ለዓየር ንብረት ለውጥ ዓይነተኛ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አንስተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ያስተናገደው ድርቅ የዚሁ የዓየር ንብረት ለውጥ ውጤት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያም የዓየር ንብረት ለውጥ የውሃ ምንጮችን አድርቋል፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎችም የድርቅ አደጋን አስከትሏል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ዓለም እየተሰቃየ ያለበትን ይህን ችግር ለመፍታት ከስብሰባዎች ያለፈ ተግባራዊ መፍትሄ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መክረዋል።
እንዲህ ዓይነቱን ተግባራዊ መፍትሄን በመውሰዱ ኢትዮጵያ ውጤታማ ሆና ትጠቀሳለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በ2011 ዓመተ ምህረት ላይ ተፋሰስን ለማልማት፣ የደን ሽፋኗን ለመሳደግ፣ ኢኮቱሪዝምን ለማስፋፋት እና የከተሞቿን የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን መጀመሯን አስታውሰዋል።
ለአራት ዓመት በሚቆየው ዘመቻ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ወጥና ብትነሳም፥ ዜጎቿ 25 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ካስቀመጡት ግብ በላይ መፈፀማቸውን ነው የጠቆሙት።
25 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንም ችግኝ በማፍላት፣ የችግኝ ጉድጓድ በመቆፈር እና የተተከለውን በመንከባከብ መሳተፋቸውም በመልዕክታቸው ተጠቁሟል።
የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ስኬታማነት ማሳያዎች ብለውም፥ ዘመቻው ሲጀመር 40 ሺህ ብቻ የነበሩት የችግኝ ማፍያዎች አሁን ላይ ወደ 121 ሺህ በማደግ በዓመት 7 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኝ የማፍላት አቅም ላይ መድረሳቸውን ዘርዝረዋል።
ለችግኝ ተከላ የሚያስፈልጉ ቦታዎችን በመምረጡ እና ለተከላ በማዘጋጀቱ ረገድም የታየው እምርታም ሌላው ምሳሌያቸው ነው።
በዚህ ስኬት ውስጥ የፖለቲካ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ቁልፍ ሚና መጫወቱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገለፁት።
አሁንም ብዙ ስራ ቢጠበቅም በሀገሪቱ አረንጓዴ ባህልን በመፍጠሩ ረገድ ዘመቻው እንደተሳካ ጥርጥር የለንም ብለዋል።
በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች አሁን ላይ የአረንጓዴ ስፍራ አስፈላጊነትን ተረድተው ቦታ እያዘጋጁለት መምጣታቸው ለተፈጠረው አረንጓዴ ባህል ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ አረንጓዴ ባህል ለቀጣዩ ትውልድም የሚቆይ መሆኑንም አንስተዋል።
አረንጓዴ ባህልን ከመፍጠር ባለፈ ዘመቻው ለ767 ሺህ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ያበረከተውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦም አመልክተዋል።
ይህ የኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ጥረት ለዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ ሰበብ የሆነውን የበካይ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ አንዱ መፍትሄ መሆኑን አስታውሰዋል።
የታዳሽ ሃይል በሆኑት የውሃ፣ ንፋስ፣ ፀሃይ እና የእንፋሎት የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የምታውለው መዋዕለ ንዋይ ሌላው የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በበኩሏ እየተወጣች የምትገኘው ሀላፊነት መሆኑን ነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት የተብራራው።
አፍሪካ ብሎም ዓለም ተፅዕኖው እየከፋ የመጣውን የዓየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እንዲህ ዓይነቱን ተግባራዊ መፍትሄ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይ የአፍሪካ ሀገራት በዓየር ንብረት ለውጥ ችግር ላይ ለሚወያዩ ስብሰባዎች መዋዕለ ንዋያቸውን ከሚያፈሱ ይልቅ፥ ለችግኝ ተከላ ስራዎች እንዲያውሉ ጠይቀዋል።