Israeli warplanes bombed a 5-storey residential house near Al-Shifa Hospital in Gaza, Palestine, on August 6, 2022(Photo by Momen Faiz/NurPhoto)

ዓለምአቀፋዊ ዜና

በጋዛ ሰርጥ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረሰ

By Alemayehu Geremew

August 08, 2022

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራዔል ከፍልስጤም ታጣቂዎች ጋር በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም ሥምምነት ላይ መድረሷን አስታውቃለች፡፡

በግብጽ አደራዳሪነት ትናንት የተደረሰው የተኩስ አቁም ሥምምነት በአካባቢው ሠዓት አቆጣጠር ከትናንት ምሽት 11 ሠዓት ከ30 ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል ነው የተባለው፡፡

ሥምምነቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲደረግ የነበረውን የአየር ድብደባ እና የሮኬት ጥቃት የሚያስቆም ነውም ተብሎለታል፡፡

እስራዔል የዜጎቿ የዕለት ከዕለት ሕይወት ሠላም መሆን እንደሚያሳስባት ገልጻ የሠላም አውርድ ሥምምነቱ ከተጣሰ እና በድጋሚ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች፡፡

ሁለቱ ወገኖች ሥምምነት ላይ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ የፍልስጤም ታጣቂዎች እስራዔል ላይ የፈጸሙት የሮኬት ጥቃት 96 በመቶ ያህሉ በፀረ-ሚሳዔል መክሸፋቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

እስራዔልም የታጣቂዎቹ መሪ ይገኝበታል ባለችው በጋዛ በሚገኝ አንድ ኅንጻ ላይ በወሰደችው አጸፋዊ የአየር ድብደባ ታይሲር አል-ጃባሪን የተባለውን የጦር አዛዥ ገድላለች፡፡

በወሰደችው ተጨማሪ የአየር ላይ ጥቃትም የታጣቂዎቹን የአቅርቦት መጋዘኖች እና መከታተያ ቦታዎች ያወደመች ሲሆን ሌላ ስሙ ያልተገለጸ ከፍተኛ መሪም መግደሏም ተዘግቧል፡፡