Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም በበጀት አመቱ ከ372 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ2014 በጀት አመት ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ከ372 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨቱን ገልጿል፡፡

የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ ለ2 ሺህ 633 የብድር ተጠቃሚዎች 372 ሚሊየን 140 ሺህ 265 ብር ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ብድር ተሰራጭቷል፡፡

በጥቃቅና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 2 ሺህ 310 ኢንተርፕራይዞች ከ358 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም በማሽነሪ ሊዝ ለ35 ተበዳሪዎች 26 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ብድር ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡

ተቋሙ ገንዘብ ማበደር ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰቡ የቁጠባ ባህል እንዲያድግ በትኩረት እንደሚሰራና በዚህም ከ228 ሚሊየን ብር በላይ በቁጠባ ማሰባሰቡ ተገልጿል፡፡

ተቋሙ ስራ ለመጀመር እየፈለጉ በገንዘብ እጥረት ያሰቡትን ማሳካት ላልቻሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብ አቅርቦት ረገድ የሚያጋጥማቸውን ችግር እየፈታ እንደሚገኝም ነው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው የተናገሩት፡፡

82 በመቶ የሚሆኑት የብድር ተጠቃሚዎች ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት ከ52 ሺህ የሚበልጡ የብደርና ቁጠባ ደንበኞች አሉት ብለዋል፡፡

ከድሬዳዋ ከተማ ውጪ በሀረርና በጂግጂጋ ከተሞችም ቅርንጫፍ ከፍቶ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት እየሠጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version