Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቀድሞው የቡርኪናፋሶ መሪ ብሌዝ ኮምፓውሬ የቶማስ ሳንካራን ቤተሰቦች ይቅርታ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 20፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ቶማስ ሳንካራን አስገድለዋል በሚል የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው የቀድሞው የቡርኪናፋሶ መሪ ብሌዝ ኮምፓውሬ የሟቹን ፓን አፈሪካኒስት ቤተሰብ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ኮምፓውሬ ለሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ሊዮኔል ቢልጎ በላከው መልዕክት ÷ በሥልጣን ዘመኔ ለፈፀምኳቸው ተግባራት የቶማስ ሳንካራን ቤተሰቦች እንዲሁም የቡርኪናፋሶን ህዝብ ይቅርታ እንዲያደርግልኝ እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ ጥቅምት 15 ቀን 1987 ቶማስ ሳንካራን በማስገደል  መንበረ-ሥልጣኑን የተቆናጠጡት  ብሌዝ ኮምፓውሬ የምዕራብ አፍሪካዋን ሀገር ቡርኪናፋሶ ለ30 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡

የቀድሞውን ፕሬዚዳንት የኦጋድጉ ፍርድ ቤት በቶማስ ሳንካራ ግድያ ጥፋተኛ ናቸው ካለ በኋላ እርሳቸው እና ተባባሪዎቻቸው ጊልበርት ዳይንደርሬ እና ካፋንዶ ሃይሲንቴ ላይ የዕድሜ ልክ እሥራት መበየኑን አፍሪካ ኒውስ አስታውሶ  ዘግቧል፡፡

Exit mobile version