አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ፈተናዎችን በመቋቋም ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ፡፡
መንግስት ባለፉት ሦስት አመታት የኮቪድ-19፣ የግጭት፣ የድርቅና የዋጋ ግሽበት ፈተናዎችን በመቋቋም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን በማሳካት ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስገንዘቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ከልማት አጋሮች ጋር በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በአካልና በበይነመረብ የተካሄደውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትረስት ፈንድ ካውንስል የውይይት መድርክ በትናንትናው እለት ሲከፍቱ እንደገለጹት፥ ምንም እንኳን ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ባለፉት አመታት የኢኮኖሚ እድገቱን በማስቀጠል፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ምህዳር በመፍጠር፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳዳግ ዘላቂ የስራ እድል በመፍጠር፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት በማሻሻልና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል ተስፋ ሰጪ ለውጦች መታየት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡
የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከሚለግሱት ገንዘብ በተጨማሪ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳውን ለመደገፍ እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም ቃል ከገቡት ገንዘብ ውስጥ በ7 ሚሊዮን ዶላር የ12 ፕሮጀክቶች ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን አቶ አህመድ ጠቅሰው፥ የስራ እድል ፈጠራን፣ እድገትን፣ የግሉን ዘርፍ ሚናን በማሳደግ ረገድ ፋይዳ ያለውን እንዲሁም ከ10 አመቱ መሪ የልማት እቅዱ ጋር የተናበበው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እውን እንዲሆን እስካሁን ላበረከቱት የገንዘብና ቴክኒካዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአለም ባንክ አስተባባሪነት ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትረስት ፈንድ ካውንስል የመንግስት ኢንቨስትመንት አስተዳደር፣ የህዝብ ሀብት አስተዳደር፣ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ማዘመን ላይ ያተኮሩ 9 የቴክኒክ ድጋፎች በ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በጀት ወደ ተግባር እንዲገቡ ወስኗል፡፡
በአለም ባንክ እየተዳደረ ላለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትረስት ፈንድ ገንዘብ ያዋጡ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ እና የጀርመን መንግስታት ተዋካዮች በስብሰባው ላይ መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።