የሀገር ውስጥ ዜና

ባለስልጣኑ በ2015 በጀት ዓመት ከቡና ምርት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ገለጸ

By Amele Demsew

July 26, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት የቡና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ከፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷በበጀት ዓመቱ 320 ሺህ ቶን ቡና ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት በመላክ የተቃደውን ገቢ ለማሳካት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውጤታማ ያደረጉ አሰራሮች ቢኖሩም እንደ ክፍተት የተለዩ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ÷ የተስተዋሉ ክፍተቶቹን መሙላት የሚያስችል ስርዓት እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

በተለይም በአቅራቢዎች እና ላኪዎች መካከል ያሉ ጉድለቶችን ሊሞላ የሚችል የኦንላይን አሰራር በ2015 በጀት ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነው ያስረዱት

ባለስልጣኑ ከቡና ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመዋል፡፡

ቻይናን ጨምሮ የኢትዮጵያ ቡና በስፋት ሊቀርብባቸው የሚችሉ እና የገበያ እድል ያለባቸው ሀገራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው÷ተጨማሪ 33 ሀገራት ላይ ምርቱን የማስተዋወቅና ገበያ የማፈላለግ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

የቡና ምርታማነትን ለማሳደግም ከ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ያረጁ የቡና ተክሎች በአዲስ መተካታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በጥራት ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማስጠበቅ የሚችሉ የቡና አመራረት ስርዓቶችን ለቡና አምራቾች የማስተማሩ ስራ በስፋት መከናወኑንም አብራርተዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!