Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ላሳዩት ሀገራዊ አንድነትና ላስገኙት ውጤት የጀግና አቀባበል ይደረግላቸዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላሳዩት ሀገራዊ አንድነትና ላስገኙት ወርቃማ ድል ልዩና ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአሜሪካ በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ነገ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በሻምፒዮናው ላይ የተሳተፈውን የልዑካን ቡድን አቀባባል በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷ ለኢትዮጵያ አኩሪ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶችና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸውም ነው የገለጹት።

የአቀባበል ዝግጅቱ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ሲሆን÷ የመጀመሪያው በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የልዑካን ቡድን የሚደረገው አቀባበል ነገ ምሽት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የሚከናወን ይሆናል ነው የተባለው፡፡

በሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በአዲስ አበባ የተመረጡ ቦታዎች ላይ ሕዝቡ ለአትሌቶቹ አድናቆቱን በመግለጽ የጀግና አቀባበል እንደሚያደርግላቸው ተገልጿል።

ልዑካን ቡድኑ ሐሙስ ዕለት ከስካይ ላይት ሆቴል በመነሳት በእስጢፋኖስ፣በአራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ቸርችል ጎዳና መስቀል አደባባይ ዞሮ ወደ ቤተ መንግሥት ካቀና በኋላ÷ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር እንደሚከናወን በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በዳንኤል እንዳለ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version