Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሶማሌ ክልል መንግስት የ2015 ረቂቅ በጀት ከ31 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ካቢኔ ባካሄደው 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2015 ዓ.ም የክልሉ መንግስት ረቂቅ በጀት 31 ቢሊየን 687 ሚሊየን ብር እንዲሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ አፀደቀ።

በሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን ስብሳቢነት በተካሄደው የካቢኔ ስብሰባ አራት አጀንዳዎች የቀረቡ ሲሆን፥ ካቢኔው የቀረቡለትን አጀንዳዎች በሙሉ ድምፅ በመቀበል እንዲፀድቁ ወደ ክልሉ ምክር ቤት መርቷቸዋል።

በዚሁም መሰረት የክልሉ የ2015 ረቂቅ በጀት 31 ቢሊየን 687 ሚሊየን 160 ሺህ 384 ብር እንዲሆን በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል።

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል የሕግ አገልግሎት ምዝገባና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ፣ የዱር እንስሳት ሀብት ጥበቃና ልማት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም በክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው በመወያየት ለምክር ቤቱ ቀርበው እንዲፀድቁ በሙሉ ድምፅ ውስኗል።

በዘንድሮው በጀት አመት በክልሉ ለመሰብሰብ የታቀደው ገቢ 9 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ ይህም በ2014 በጀት አመት ከተሰበሰበው ገቢ የ18 በመቶ ብልጫ እንዳለውና ለ2015 የቀረበው ረቂቅ በጀት ከ2014 በጀት ጋር ሲነፃፀርም የ8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

ለ2015 ከተያዘው ረቂቅ በጀት 28 በመቶው በክልሉ በሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን ሲሆን፥ ቀሪው 72 በመቶ ደግሞ ከፌደራል መንግስት በሚገኝ ድጎማ እንደሚሸፈን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version