የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥድስት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን አስተዋወቀ

By Amele Demsew

July 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2014 ዓ.ም በአዴት እና ደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከላት የተጠኑ ሥድስት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን አስተዋውቋል ፡፡

የምርምር ተቋሙ÷ በጤፍ ሁለት ዝርያዎች፣ በምግብ ገብስ፣ በዳቦ ስንዴ፣ በዳጉሳ እና በምግብ ሲናር ላይ የተደረገው ጥናት በእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ዝርያን በማሻሻል በድምሩ ሥድስት ዝርያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ መለቀቃቸውን አስታውቋል።

የተለቀቁት ሁሉም ዝርያዎች በብሄራዊ የዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው አስፈላጊውን የዝርያ አለቃቀቅ መስፈርት አሟልተው መለቀቃቸውን ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተቋሙ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በአርሶ አደር ማሳና በምርምር ጣቢያ ባደረገው የዝርያ መረጣ ጥናት መሰረት ምርታማነትን መጨመር፣ ጥራታቸውን፣ ድርቅና በሽታ መቋቋምን ማዕከል አድርጎ የአምስት ሰብሎች አዳዲስ ዝርያዎች አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረጉ ይታወሳል።