የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ተምች መከሰቱ ተገለጸ

By Melaku Gedif

July 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ተምች መከሰቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው እንዳሉት÷ በበሀገረማርያም፣ ምንጃር፣ በረኸት አሳግርት፣ አንጎለላና ጠራ፣ አንኮበርና መንዝቀያ በሚገኙ 50 ቀበሌዎች ላይ ነው ሰሞኑን ተምች የተከሰተው፡፡

ተምቹ በተከሰተባቸው ወረዳዎች የጸረ ተባይ ኬሚካል እየተሰራጨና ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ነው ቡድን መሪው የተናገሩት፡፡

አርሶ አደሩ ጸረ -ተባይ ኬሚካሉን በመጠቀም እና በባህላዊ መንገድ ነፍሳቱን በመጨፍጨፍ እንዲሁም ባለሀብቶች ኬሚካል በማቅረብ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ድሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች በበኩላቸው÷ ተምቹ በገብስና በቆሎ ሰብሎቻቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይም በጸረ- ተባይ ኬሚካል ርጭትና በባህላዊ መንገድ ተምቹን ለመከላከል እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በታለ ማሞ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!