አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጄክት እቅዷን በአግባቡ እተገበረች መሆኗን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር ገለፁ፡፡
አምባሳደሩ ከኩሳላ ግሪን ባዮዳይቨርሲቲ ድርጅት መስራች እና ዳይሬክተር ጋር በአየር ንብረት ለውጥና በአፍሪካዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ሙክታር በውይይታቸው፥ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥና ብክለት ዝቅተኛ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያላት ሀገር ሆና ሳለ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ መሆኗን ነው ያስረዱት፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድርግ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጄክት እቅድ አውጥታ እየተገበረች መሆኗን እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ ጥቂት አገራት አንዷ እንደሆነችም አብራርተዋል፡፡
የእድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥም የኃይል አቅርቦት ማሳደግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የታዳሽ ኃይል አቅም ያላት አገር መሆኗንም ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ መሪዎች ተነሳሽነት በተጀመረውና እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ18 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ልምድ በማስፋፋት የምሥራቅ አፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለመታደግ የተቀናጀ ጥረት እየተካሄደ ነው ሲለ አምባሳደር ሙክታር መናገራቸውን ከፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገነነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!