የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለዓለማቀፉ የፀረ-ሽብርተኝነት አካዳሚ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

By Meseret Awoke

July 13, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለዓለማቀፉ የፀረ- ሽብርተኝነት አካዳሚ ጠንካራ ድጋፍ እንደምታደርግና ከአካዳሚው ጋር በቅርበት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት የዓለምአቀፉ ፀረ-ሽብርተኝነት አካዳሚ ድጋፍና ልገሳ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ በፓሪስ በተካሄደው ጉባዔ ነው፡፡

በጉባዔው ላይ በበይነ መረብ በኩል ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ ኢትዮጵያ ከአካዳሚው ጋር ለመስራት እንዲሁም አካዳሚው የሚያስፈልገውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጰያ ሽብርተኘነትን በመዋጋት ረገድ ጠንካራ የሆነ አቋም እንዳላት የገለጹ ሲሆን ፥ በምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንዲሁም ሰላም እና ደህንነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ መሰዋእትነት መክፈሏን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከከፈለችው መስዋእትነት መካከል በሱማሊያ አል-ሻባብን ለመዋጋት በተደረገው የሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ በመሳተፍ ሶማሊያ ውጤታማ የሆነ ሀገራዊ ምርጫ እንድታካሂድ ማስቻሏን እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡

በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን ሽብርተኝነት በመገንዘብ ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ መንግስታት፣ በአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ቀጠናዊ ስልቶች የበለጠ ቅንጅት ሊኖራቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጉባኤው ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተጋበዙ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ድኤታዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተሳትፈዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!