አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6 ፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ጃፓን የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የምግብ እርዳታ ፕሮግራም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የእርዳታ ስምምነቱ በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ተፈርሟል፡፡
በእርዳታ ስምምነቱ በድርቅ፣ በግጭት እና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች የሚያጋጥማቸውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል፥ 2 ሺህ 250 ቶን የጃፓን ሩዝ ለኢትዮጵያ ይቀርባል።
የሩዝ ድጋፉ የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባሻገር ከውጭ በግዥ የሚገባውን የሩዝ ምርት በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ለመቆጠብ አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ጃፓን ከ2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ዋና ትኩረት የሆነውን የሩዝ ምርት እንዲሻሻል ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡