ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአሜሪካ የባሕር ጦር መርከብ የቻይናን ግዛት ጥሶ መግባቱ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

July 13, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት የአሜሪካ የጦር መርከብ ከቻይና መንግስት ፈቃድ ውጪ በደቡብ ቻይና ባሕር በሚገኙ ደሴቶች አካባቢ መግባቱን የቻይና ጦር አስታወቀ፡፡

የቻይና ጦር የደቡብ ዕዝ ቃል አቀባይ ቲያን ጁንሊ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ በቀጠናው የታየው የአሜሪካ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የቻይናን ሉዓላዊነትና የሠላም ፍላጎት የሚጋፋ ነው ብለዋል፡፡

ቲያን ጁንሊ በቻይና ግዛት ውስጥ የተስተዋለው የአሜሪካ የባሕር ጦር እንቅስቃሴ የደቡብ ቻይናን ባሕር ሠላምና መረጋጋት የሚጎዳ፣ ዓለም አቀፍ ህግጋትን እና የዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን ኅግ የጣሰ ነው ሲሉም በመግለጫቸው ተናግረዋል።

“አሜሪካ በደቡብ ቻይና ባሕር አካባቢ የፈጸመችው ጥሰት የደኅንነት ሥጋት ፈጣሪ እና የአካባቢውን ሠላም እና መረጋጋት አጥፊ መሆኗን ያረጋገጠ ተግባር ነውም” ብለዋል – ቃል አቀባዩ፡፡

የቻይና ጦር የሀገሪቷን ሉዓላዊነት፣ ደኅንነት ፣ ሠላም እና መረጋጋትን ለመጠበቅ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ እንደሚገኝ ማስታወቁንም ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡