አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በቦይን 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦችና ወዳጆች 1ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር አካሄዱ።
የመታሰቢያ መርሃ ግብሩን በዛሬው እለት የአውሮፕላን አደጋው በደረሰበት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ቱሉፋራ ቀበሌ ላይ የሟቾች ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት ነው የተካሄደው።
በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ የሟቾች ቤተሰቦችም ተገኝተዋል።
የዛሬ አንድ ዓመት ልክ በዛሬዋ ቀን ነበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ድንገት የተከሰከሰው።
በአደጋውም በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 149 መንገደኞች እና 8 የበረራ ሰራተኞች በድምሩ ከ33 ሀገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውም አይዘነጋም።
የአደጋውን መንስኤ የማጣራት ስራም ተካሂዶ ችግሩ የአውሮፕላኑ የሶፍትዌር ችግር መሆኑ መገለፁ የሚታወስ ነው።
የአውሮፕላን አደጋውን መንስኤ ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን ትናንት ጊዜያዊ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው የአደጋ ምርመራ ውጤት በአጠቃላይ የአውሮፕላኑ የዲዛይን ችግር የአደጋው መንስኤ መሆኑን አረጋግጧል።