አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ጨምሮ የሦስት ሀገራትን የዕዳ ተጋላጭነት ለመፍታት አሜሪካ ፍላጎት እንዳላት የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ፓትሪሺያ ፖላርድ አስታወቁ፡፡
በፓሪስ ጉባዔ እየተሳተፋ የሚገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ከመደበኛው ጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ፥ ከፓሪስ ክለብ ተባባሪ ሊቀመንበር ዊሊያም ሮስ ጋር ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የብድር ሽግሽግ ጥያቄ መሰረት በማድረግ የአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴው እስካሁን ስላከናወነው ተግባር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ተባባሪ ሊቀመንበሩ ዊሊያም ሮስ ፥ ኮሚቴው እስካሁን ሦስት ጊዜ ተገናኝቶ እንደመከረ አስታውሰው ፥ አራተኛውን ስብሰባ በቅርቡ እንደሚያደርግና ከዚህ በፊት በተደረጉት ውይይቶች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ከኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ከገዙ ባለሀብቶች ጋር ምክክር ያደረጉ ሲሆን ፥ ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ባለሃብቶቹ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የዕዳ አገልግሎት ግዴታዎችን ለማክበር የምታደርገውን ጥረትና የዕዳ ተጋላጭነቷን በመቆጣጠር ረገድ ያሳየችውን የገበያ ዲሲፕሊን አድንቀዋል፡፡
ዶ/ር እዮብ ፥ ኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ በተጨማሪ አሁን ላይ የሚስተዋሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን በመቅረፍ ኢትዮጵያ በቀጣይ ጊዜ ወደ ብድር ገበያ የመመለስ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትር ዴኤታው ከአሜሪካ የገንዘብ ምክትል ሚኒትር ፓትሪሺያ ፖላርድ በዕዳ አያያዝ የጋራ ማዕቀፍ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በአበዳሪዎች ኮሚቴ የታየው ከፍተኛ እድገትና የፓሪስ ክለብ መሪዎች ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን የፋይናንስ ዋስትና ለመስጠት ያደረጉት አጠቃላይ ጥረት ለገንዘብ ምክትል ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
ፓትሪሺያ ፖላርድ በበኩላቸው ፥ የጋራ ማዕቀፉ እንዲሳካና እስካሁን ባለው የጋራ ማዕቀፍ የእዳ ሽግሽግ የጠየቁትን ኢትዮጵያን ጨምሮ የሦስት ሀገራትን የዕዳ ተጋላጭነት ለመፍታት አሜሪካ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡