አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው ዘርፍ ለአፍሪካ ልማት አጋዥ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ኤግዚቢሽን በጣሊያን ቦሎኛ ሊካሄድ መሆኑን በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ አስታወቋል።
በአዲስ አበባ የጣሊያን ኢምባሲ የንግድ ማስታወቂያ ክፍል ዳይሬክተር ሪካርዶ ዙኮኒ እና የጣሊያን የግብርና መሳሪያዎች አምራች ፌዴሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክር ፋቢዮ ሪቺ፤በጉዳዩ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሪካርዶ ዙኮኒ በመግለጫቸው÷ የኤግዚቢሽኑ ዋነኛ አላማ በግብርና ልማት ዘርፍ የቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥ በማድረግ የተሻለና ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኤግዚቢሽኑ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበት አጋጣሚ የሚፈጠር መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያም በዘርፉ ልማት የተሰማሩ ኩባንያዎች፣አምራች ማህበራት እና ሌሎችም በኤግዚቢሽኑ ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ እድገት የተሰጠውን ትኩረት ያደነቁት ዳይሬክተሩ÷ በቦሎኛ በሚካሄደው ኤግዚቢሽን መንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።
የጣሊያን የግብርና መሳሪያዎች አምራች ፌዴሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋቢዮ ሪቺ፤ኤግዚቢሽኑ በግብርና ምርቶች የተሻለ የማምረት አቅም ያላቸው አገራት ልምዳቸውን የሚያጋሩበት እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በጣሊያን የሚመረቱ መሳሪያዎችም ሆኑ በተለያዩ ዓለም አገራት የሚመረቱ መሳሪያዎችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችና የግብርና መሳሪያ አስመጪዎች በኤግዚቢሽኑ ይሳተፋሉ ብለዋል።