የሀገር ውስጥ ዜና

በ2014 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሐረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ

By Shambel Mihret

July 11, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሐረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የሀረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን እንደገለጹት÷ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚታቀዱ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ በተለይም ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ ነው።

ለዚህም በተጠናቀቀው የበጀት የክልሉን ገቢ አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር ዘርፈ ብዙ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።

በ2014 ዓ.ም 1 ቢሊየን 64 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ቢሊየን 130 ሚሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል።

ገቢው በቀጥታ ታክስ 587 ሚሊየን ብር፣ ቀጥታ ካልሆነ ታክስ 327 ሚሊየን ብር፣ ታክስ ነክ ካልሆነ ገቢ 77 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ደግሞ 137 ሚሊየን ብር የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ገቢው ከ2013 ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ39 በመቶ ወይም ከ317 ሚሊየን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።

በ2015 የበጀት ዓመትም ከግብር ከፋዩና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የክልሉ ኢንቨስትመንት ፣ ማእድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ያህያ እንደገለፁት÷ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 89 ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንትን ዘርፎች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ለገቡ ባለሀብቶች የድጋፍና የክትትል የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት 129 በባለሃብቶች አማካኝነት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተደረገ ቁጥጥርና ክትትልም ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ 17 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው÷ ወደ ስራ ባልገቡ 18 ባለሀብቶችም ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም አብራርተዋል።

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!