ዓለምአቀፋዊ ዜና

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊየን እንደሚደርስ የተመድ ትንበያ አመላከተ

By Alemayehu Geremew

July 11, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ሕዳር ወር አጋማሽ የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊየን እንደሚደርስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትንበያው አመላክቷል።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ÷ፕላኔታችንን በመንከባከብ የጋራ ኃላፊነታችንን እንወጣ ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።

ብዝኃነታችንን አክብረን ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መሥጠት ይገባናልም ብለዋል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፡፡

ዋና ጸኃፊው ፣የዓለም ጤና ክብካቤን በተመለከተ መሻሻል እንዳለና የዕድሜ ማራዘሚያ መድሃኒቶች እና ለእናቶችና ሕጻናት የሚደረጉ ክብካቤዎች በመጨመራቸው ምክንያት የሰው ልጆች ሞት በእጅጉ መቀነሱን ጠቁመዋል።

የተመድ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ክፍል የዓለም ህዝብ ቁጥር ከፈረንጆቹ 1950 ጀምሮ በዝቅተኛ ፍጥነት እያደገ እንደነበረ አመላክቷል።

በፈረንጆቹ 2030 የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ነጥብ 5 ቢሊየን እንዲሁም በፈረንጆቹ 2050 ደግሞ 9 ነጥብ 7 ቢሊየን ይደርሳል የተባለ ሲሆን በ 2080ዎቹም ወደ 10 ነጥብ 4 ቢሊየን እንደሚደርስ ትንበያው ያመላክታል።