የከተማ አስተዳደሩ የ20/80 ባለሶስት መኝታ የጋራ መኖርያ ቤት እጣ አለመውጣትን አስመልክቶ ማብራርያ ሰ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ የ20/80 ባለሶስት መኝታ የጋራ መኖርያ ቤት እጣ አለመውጣትን አስመልክቶ ማብራርያ ሰጠ።
የአስተዳደሩ ማብራሪያ ሙሉ ቃል እንደሚከለው አቀርቧል፦
የ20/80 ባለሶስት መኝታ የጋራ መኖርያ ቤት እጣ አለመውጣትን አስመልክቶ የተሰጠ ማብራርያ!
እንደሚታወቀው የከተማ አስተዳደሩ ባሳለፍነው ሳምንት የ20/80 የ14ኛ ዙር የ40/60 3ኛ ዙር የጋራ መኖርያ ቤት እጣ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ በ20/80 ፕሮግራም የባለሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በእጣው አለመካተትን መነሻ በማድረግ ከአንዳንድ ግለሰቦች የደረሰንን የግልፅነት ጥያቄ አስመልክቶ የሚከተለውን ማብራርያ ለማቅረብ እንወዳለን፡-
👉 በዚህ ዙር ለ20/80 የቤት ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ እጣ የወጣባቸውና የተስተናገዱት የ1997 ተመዛጋቢዎች ብቻ ናቸው፡፡
👉 የ2005 የ20/80 ተመዝጋቢዎች ግን ከስቱዲዮ ጀምሮ ባለአንድ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ በሙሉ በእጣ ውስጥ አልተካተቱም፡፡
👉 የ40/60 የቤት ፕሮግራም ግን በ2005 ዓ.ም ብቁ የሆኑ ሙሉ ለሙሉ በእጣ ተካተው በዚህ ዙር የእጣ አወጣጥ በ40/60 ባለአንድ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ ቤቶች እጣ እንደወጣላቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡
👉 ስለሆነም በዚህ ዙር ያልተስተናገዱት 1997 ዓ.ም የተመዘገቡ ባለሶስት መኝታ ተመዝጋቢዎች ብቻ ናቸው፡፡
👉 ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በ12ኛ ዙር እጣ የ1997 ባለሶስት መኝታ ተመዝጋቢዎችን ሙሉ ለሙሉ አስተናግደናል በሚል መነሻ መረጃቸው የተሟላ የሆኑት ተስተናግደው የባለሶስት መኝታ ፕሮግራም ተዘግቶ ነበር፡፡
👉 ከዚህ በኋላ በ1997 ተመዝጋቢዎች ውስጥ በ20/80 ባለሶስት መኝታ እጣ ሊወጣለት የሚችል ተመዝጋቢ የለም በሚል ቤቶቹን በሚያስተዳድረው ቦርድ ውሳኔ ፕሮግራሙ ከሲስተም ውጪ እንዲሆን ተደርጓል።
👉 በዚህም ምክንያት በዚህኛው(በ14ኛ) ዙር እጣ ማስተናገድ አልተቻለም::
ነገር ግን ከተዘጋ በኋላ ከባንክ የተገኘው መረጃ ጥቂቶች ቢሆኑም ቁጠባ በመቀጠላቸው ብቁ የሆኑ ጥቂቶች ተገኝተዋል::
👉 በአሁን ሰአትም ምዝገባው ከባንክ በሚወሰድበት (በሚከለስበት ወቅት) በተገኘው መረጃ ከ1997 ተመዝጋቢዎች መሃከል ጥቂት ሰዎች በአግባቡ እየቆጠቡ ያሉና ብቁ የሆኑ የ20/80 ተመዝጋቢዎችን ማግኘት ተችሏል፡፡
👉 ስለሆነም አስተዳደሩ እነኚህን ተመዝጋቢዎች ምንም እንኳን ፕሮግራሙ በይፋ የተዘጋ ቢሆንም ከባንክ በተገኘው መረጃ መሰረት በአግባቡ እስከቆጠቡ ድረስ ማስተናገድ እንደሚገባ ያምናል፡፡
👉 ነገር ግን ከመረጃ ውስንነትና በሲስተሙ ላይ የሚያስከትለውን ተጨማሪ የመረጃ መመሰቃቀል ለመከላከል ሲባል ወደ በኋላ ተመልሶ ሲስተሙን ለቀሩት ጥቂት ቆጣቢዎች ብቻ መክፈት አስፈላጊ ሆኖ ባለመገኘቱ ምክንያት እነዚህን ተመዝጋቢዎች ለብቻቸው በልዩ ሁኔታ ልናስተናግድ ይገባል የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡
👉 ስለሆነም የ1997 ተመዝጋቢ ሆናችሁ ባለሶስት መኝታ ቤቶች በአግባቡ የቆጠባችሁ አስተዳደሩ በሚያወጣው ፕሮግራም በልዩ ሁኔታ የምትስተናገዱ መሆኑን እያሳወቅን ፤ ህብረተሰቡ ይህንን አስመልክቶ አንዳንድ የሚናፈሱ የተሳሳቱ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን!!
👉 በተጨማሪም ዘርፉን የሚመሩ አመራሮች ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ ሚድያዎች የሚያደርሱ መሆኑንም እናሳውቃለን!!