አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በአራት የወንጀል ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የነበረው የፖሊስ አባል በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ፡፡
ተከሳሽ ረዳት ሳጂን አሸናፊ ጫካ በመጀመሪያ ለጥበቃ በተሰጠዉ የጦር መሣሪያ አይሱዙ የጭነት መኪና በማስቆም የመኪናውን አሽከርካሪ ተኩሶ በመግደሉ ክስ ተመስርቶበታል፡፡
በተጨማሪም ተከሳሹ የግል ተበዳዮች የሆኑትን መሀመድ ኡስማንና አደም አህመድ የተባሉትን የአካባቢው ነዋሪዎች በስራ ላይ እያሉ ለምን ዘፈን ታዳምጣላችሁ በማለት ሙዚቃ ወደሚሰማበት አቅጣጫ ጥይት ተኩሷል፡፡
እንዲሁም በግል ተበዳይ ወንድሙ ዓለሙ ላይ በውል በማይታወቅ ምክንያት በጀርባዉ እና በቀኝ እጁ ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፥ በአራተኛው ክስ ደግሞ የግል ተበዳይ ዘመድኩን አለኸኝን ተከሳሽ በያዘው የጦር መሣሪያ በመደብደብ በጀርባውና በቀኝ ዓይኑ ላይ ጉዳት ማድረሱን የቤንች ሸኮ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ክስ መስርቶበታል፡፡
ክሱን ሲመለከት የቆየው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን በመመልከት ተከሳሽ ረዳት ሳጂን አሸናፊ ጫካ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ዉሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቢንያም ባቡ ዉሳኔውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አንዳንድ ለሙያቸዉ ክብር የሌላቸዉና ከሕዝቡና ከመንግሥት የተሰጣቸውን አደራ የማይወጡ የፖሊስ አባላት ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለዋል፡፡
ወንጄልን ለመከላከል በሚከናወኑ ተግባራት የአካባቢው ማህበረሰብ ከመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት መሥራት አለበት ያሉት ዳኛ ቢንያም ባቡ፥ ሕዝብን ለመጠበቅ አደራ የተሰጣቸው የፀጥታ አካላትም የመንግሥትና የሕዝብ አደራን መጠበቅ እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ከቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።